ሐገራችን ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ልካ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ምርቶች ውስጥ ቆዳና ሌጦ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የቆየ ነበር።
እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው የቆዳ ገበያ ዝውውር ከ40 ቢሊየን ዶላር በላይ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሐገራችን ድርሻና ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆል በ2015 በጀት አመት በ11 ወራት ለሐገር ያስገባው የውጭ ምንዛሪ 31,000 ዶላር ብቻ እንደሆነ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንደስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል መረጃ ያሳያል።
ይህ ለምን ሆነ በሚል መነሻ በኢትዮጵያ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረና በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ሆቴል ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ በፓናሊስትነት የቀረቡት:-
ዶ/ር ሰለሞን ገብሬ በዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪ፣
አቶ ወንዱ ለገሰ በኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የሌዘር ኢኒሼሽን ፎር ሰስተኔብል ኢምፕሎይመንት ክሪኤሽን ፕሮጀክት አስተባባሪ፣
አቶ ኤርሚያስ ወሰኑ በኤሊኮ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ፣
አቶ መሐመድ ሁሴን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የእንስሳት ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ስራ አስኪያጅ ተወካይ ናቸው።
በውይይቱ ላይ በዘርፉ ያሉት ችግሮች በስፋት የተዳሰሱ ሲሆን እነዚህም
- ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠት
- ከግብአት ጋር የተያያዘ ችግር
- የውጭ ምንዛሪ እጥረት
- በዘርፉ የተማረ በቂ የሰው ሃይል አለመኖር ወይም የቆዳ ዘርፍ በትምህርት ስርዓታችን ውስጥ አለመካተቱ
- የሐይል መቆራረጥ እንደምሳሌነት የተነሱ ሲሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦችም ተጠቁመዋል።
- የከብት እርድን በቄራዎች ብቻ ማከናወን ለዚህም አነስተኛ ቄራዎችን በየአካባቢው ማስፋፋት
- ስለ ከብት እርድ በየጊዜው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ
- የቆዳ ኢኒስቲትዩቶችን ማቋቋም በትምህርት ስርዓት ውስጥም ማካተት
- መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠትና የአሰራር ሂደቱን መፈተሽ
እንደ መፍትሄ የተጠቆሙ ሲሆኑ በመጨረሻም በፓናሉ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ችግሮች እና ማነቆዎችን በጋራ ለመፍታት ተባብረሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።