በስድስት ዘርፎች የተዋቀረውና በሥሩ 44 ድርጅቶችን የያዘው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የበጀት ዓመቱን የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
ምንም እንኳን በተለያዩ የድርጅቶቻችን አካባቢዎች በርካታ ተጽዕኖዎች ቢኖሩም ይህን ተቋቁሞ የሚሰራ አመራርና ሰራተኛ በመፈጠሩ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አመርቂ ውጤት እያመጣ መሆኑን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ገልጸዋል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማህበራዊ ኃላፊነት ዳይሬክተር አምባሳደር አሊ ሱለይማን በበኩላቸው ተቋሙ ከሚሰራው የኢንቨስትመንት ሥራ በተጓዳኝ በሀገሪቱ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ አወንታዊ ምላሾችን በሚገባ የተወጣበት በጀት ዓመት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
በተለይም የሚድሮክ ድርጅቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ መስራት የተቋሙ ዋነኛ መገለጫ መሆኑንም አምባሳደር አሊ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ድርጅቶቹ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችም በበጀት ዓመቱ እንደፈተኗቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም ሀያ በመቶ የቡና ምርት ከእየ እርሻዎቹ ማሳ በተደራጁ ኃይሎች ቢዘረፍም፤ በላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንደስትሪ የፍራፍሬ ምርቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያና ሥርቆት ቢከናወንም ድርጅቱ ይህን ተቋቁሞ ከማትረፍ እንዳላገደው ግን አመልክተዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፉት 9 ወራት ከአጠቃላይ የምርት ሽያጭ ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ማግኘቱም በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡