ማዕከሉ በዚህ ዓመት እንደ ሀገር የተያዘውን 150 ሚሊየን ዶሮ የማቅረብ እቅድ ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል።
በሀዋሳ ከተማ አቅራቢያ ሻሎ እርሻ የሚገኘውን የኤልፎራ የዶሮ ልማት ማዕከል የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣ የግብርና ሚንስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ አቶ ተክሉ ጃምባ የሲዳማ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ በኢትዮጵያ የሀንጋሪ አምባሳደር አቲላ ታማሽ ኮፓኒ፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም አባ ገዳዎችና አደ ስንቄዎች በተገኙበት ተመርቋል።

የግብርና ሚነስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሮጀክቱን ያከናወነው ለትርፍ አለመሆኑንና የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ትኩረት መስጠቱን በመግለፅ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድና ድርጅታቸው ሚድሮክ ስለወሰዱት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ እንደ ሀገር የስጋ ተዋፅኦ ከውጭ በማስገባት ላይ የቆየን ሲሆን አሁን ላይ ሚድሮክ ፕሮጀክቱን በአስደናቂ ፍጥነት በማጠናቀቁና ችግሩን ለመፍታት የድርሻውን በመወጣቱ ደስታቸውን ገለፀዋል።

አያይዘውም እንደ ሀገር በ2015 ዓ.ም 40 ሚሊዮን በ2016 ዓ.ም ደግሞ 80 ሚሊዮን ዶሮዎችን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ቁጥር ሃገሪቱ ካላት አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንፃር በቂ ባለመሆኑ መሰል ስርዓቶች መዘርጋታቸው ተገቢና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ሚንስትሩ አስገንዘበዋል።
በ2017 ዓ.ም ከሌሎች ስራዎች በተጨማሪ ኤልፎራ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ስርዓትን ወደ ስራ በማስገባት እንደሀገር በአጠቃላይ 150 ሚሊዮን ዶሮዎችን በማምረት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዝግጅት መጠናቀቁን አብስረዋል።
ይህን ቴክኖሎጂ በሀገራችን ማስጀመር ቀላል ስራ ባይሆንም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ቁርጠኝነት፤ በመላ አመራሩና ሰራተኛው ብርታት መሳካቱን ገልፀው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው ማዕከሉ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ አሰራርን ባማከለ መልኩ በመዘጋጀቱ ገበያን ከማረጋጋት አንጻር ያለው ሚና ከፋተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮጅክቱ የዉጪ ምንዛሪን በማስቀረትና ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ደህንነታቸው የተጠበቁ የዶሮ ግብዓቶችን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናገረዋል።
በተጨማሪ ኤልፎራ ለስጋና እንቁላል የሚያገለግሉ ዶሮዎችን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ ወላጅ ዶሮዎችን በብዛት በማምረት ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ኤክስፖርት ለማደግ የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ታደሰ የተመረቀው ፕሮጀከት የማሕበረሰቡን በተለይም የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል አንፃር የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ገልፅዋል።

አቶ ፈለቀ በምግብ ራስን መቻል ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው በዛሬው እለት የተመረቀው ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ከ2 ወራት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው ሚድሮክ ዛሬ ያስመረቀው ይህ ፕሮጀክት የነበረዉን የዶሮ አቅርቦት ችግር ከመፍታት ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር እንደሆነና እንደ ሀገር ለተያዘው የሌማት ቱሩፋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
ሚድሮክ በልማት ብቻ ሳይሆን በድርቅ ጊዜም ከኦሮሚያና ከመላ ሀገራችን ህዝብ ጎን በመቆሙ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕን እና ሊቀ-መንበሩን ሼይክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አላሙዲንን አመስግነዋል።
የሀንጋሪ አምባሳደር አቲላ ታማሽ ኮፓኒ በበኩላቸው ሚድሮክ ፕሮጀክቱን በማሳካቱ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዉስጥ ትልቅ ታሪክ መስራት መቻሉን ገለፀዋል።
ፕሮጀክቱ በዘርፉ የሀንጋሪ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን በመገለጽ ሚድሮክ ከሀንጋሪ የግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በመስራቱና ሀገራቸውም የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል በመሆኗ ደስታቸውን ገልጸዋል።









