የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ሁሉም ዘርፎች ካለፈዉ በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምን ነሐሴ 16 እና 17/ 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሽን ሆቴል ገምግሟል።

በበጀት አመቱ የድርጅቶችን አሠራርና አደረጃጀት በማሻሻል ዉጤታማነትን የማሳደግ ተግባራት መከናወናቸውን ውይይቱን የመሩት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ገልፀዋል፡፡
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የቅድመ ወላጅ (Grandparent) ዶሮዎችን በማምጣት በኢትዮጵያ በርካታ ዶሮዎች እንዲመረቱ ለማድረግ የተጀመረውና ሰሞኑን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የሆነው ፈርቀዳጅ ስራ፣
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሞሐ የለስላሳ መጠጥ ምርቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ለማስገባት የተሰራው አመርቂ ስራና የአሰራር ስርዓት ዝርጋታ፣
በመዓድን ዘርፍ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በአካባቢ ጥበቃ የ”ISO 14001:2015 Environmental Management system” መስፈርቶችን በማሟላት ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ማግኘቱና “SPC” የወለል ንጣፍ ፋብሪካን በጣም ባጭር ጊዜ መገንባት መቻሉ፣
ኮንስትራክሽንና ሪል እስቴት ዘርፍ በመሐመዲያ ቪሌጅ ግንባታ የሚያደርገው ርብርብና የደረሰበት አመርቂ የግንባታ ደረጃ፣
የሆቴልና ሪዞርት ዘርፍ ሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሽን ሆቴል የፓን ኤዥያን ሬስቶራንት አስመርቆ ስራ ማስጀመሩ እንዲሁም
በንግድና አገልግሎት ዘርፍ 3 ተጨማሪ የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች መከፈታቸው በዚህ በጀት ዓመት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል።


ለእነዚህ ለተመዘገቡ ጉልህ ውጤቶች የአመራሩና የመላ ሰራተኛው ድርሻ ከፍተኛ እንደ ነበር ተወያዮቹ አንስተዋል።
የሁሉም ዘርፎች ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎችና የዘርፍና የየድርጅት አመራሮች በተለይም ደግሞ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ክትትልና ቁርጠኛ አመራር አይተኬ ሚና እንደነበረው ነው ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ውይይት የተገለፀው።
በዓመቱ የተገኘው አጠቃላይ ሽያጭም ካለፈው በጀት አመት ጋር ሲነፃፀር በ23 በመቶ እድገት ማሳየቱ እና በበጀት ዓመቱ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካቱም ተነግሯል፡፡
በውይይቱ ላይ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 6 ዘርፎችን የሚመሩ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችና የኮርፖሬት ዳይሬክተሮች የሚመሩትን ዘርፍና ክፍል የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡


በውይይቱ ላይም የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ሁሉም ዘርፎች የጀመሯቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች እንደተለመደው በጥሩ ጥራትና በታቀደላቸው ጊዜ እንዲያጠናቅቁ፥ እንደየዘርፎቹ ባህሪ ለሀገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙና ገቢ ምርቶችን የሚተኩ ስራዎች ላይ በተለይ አተኩረው እንዲሰሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት፣ ግብር በመክፈል ፣የሥራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የዉጭ ምንዛሬ በማስገኘት በአመቱ የነበረው አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደነበር ነው በውይይቱ የተገለፀው።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በመዓድን፣ በንግድና አገልግሎት፣ በሆቴልና ሪዞርት እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሪል ስቴት ዘርፎች የተደራጁ 45 ኩባንያዎችን ያቀፈ ተቋም ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ74 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድልም ፈጥሯል።









