ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በዚህ ዓመት በሃገር አቀፍ ደረጀ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተደረገውን ጥሪ በመቀበል በአዲስ አበባ ከተማ ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ሃይሌ ጋርመንት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 200 ሺህ ችግኞችን በማቅረብ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣የሚድሮክ ስድስቱም የየዘርፎቹ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎች፣ የአስተዳደር አካላት እንዲሁም ከ1500 በላይ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡




በአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ከአዲስ አበባ ውጭም ድርጅቶቹ ባሉበት አካባቢዎች ሁሉ በአጠቃላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ44 ኩባንያዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ከ71 ሺህ በላይ ስራተኞችን ያቀፈ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።
በዛሬው ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ ሚድሮክ እንደ ሀገር የልማት ስራዎች ላይ ግንባር ቀደም በመሆን በመሳተፉና በ2015 ”ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ 200 ሺህ ችግኞችን በማቅረቡ እናመሰግናለን ብለዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባደረገልን ጥሪ መሠረት እኛ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ቤተሰቦች 200 ሺህ ችግኝ ገዝተን በዛሬው ዕለት ”ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል በሐገራችን በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሐ ግብር ላይ የራሳችንን አሻራ ለማኖር በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ በተለይም በግሉ ሴክተር በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ይታወቃል ።
ባለፉት አምስት ዓመታትም እየተካሄዱ ባሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች ላይ የላቀ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በሚያካሂዳቸው የልማት ሥራዎች ሁሉም አካባቢን በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ ተምሳሌታዊ ሆኖ ቀጥሏል።







