ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት በ11 ከተሞች የዳቦና የዱቄት ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ቀደም ብሎ ግንባታቸው የተጀመረውና በአጋሮ፣ በወላይታሶዶ፣ በሐዋሳ፣ በጎንደር፣ በቦንጋ እና በሐረር ከተሞች የተገነቡት የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካዎች መመረቃቸው ይታወሳል፡፡
ግንባታቸውም የተከናወነውም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው፡፡

በዛሬው እለትም በጅግጅጋ ከተማ የተገነባው ፋብሪካ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው፣ አቶ ጀማል አህመድ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፣ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልሉ የስራ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከጅግጅጋ ከተማ የተውጣጡ ኡጋዞች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባሰሙት ንግግር “ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ሼይኽ መሐመድ አላሙዲ ድሮ ከነበረው አሰራር በተለየ ሁኔታ ሀብታቸውን በመላው ኢትዮጵያ ደሃ ጋር እንዲደርስ እየረዱ ስለሆነ እናመሰግናለን።

ሃብታቸውን በታማኝነት እያስተዳደሩና ለልማት እያዋሉ ያሉ አጠቃላይ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሰራተኞችን በተለይም ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድን በዚህ አጋጣሚ ላመሰግን እወዳለሁ” ብለዋል።
ቀሪዎቹ የደሴ፣ አሶሳ፣ ሰመራ እና ነቀምት ፋብሪካዎችም በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት የሚበቁ ይሆናል፡፡
ሁሉም ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው በቀን 400 ኩንታል ዱቄት እና 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም አላቸው፡፡








