ስምምነቱ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተመረጡ የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ዉጪ ሀገራት በመላክ ለሃገር ኢኮኖሚ እያደረገ ያለዉን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚረዳ ነው ።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መቀመጫውን በጀርመን ካደረገው ድርጅት ነውማን ካፌ ግሩፕ ጋር የቡና ግብይት የሁለትዮሽ ስምምነት አድርጓል።

ነውማን ካፌ ግሩፕ 60 ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈና ከ30 በላይ በሚሆኑ ሀገራት በቡና ሽያጭ ቀዳሚ ድርጅት ነው፡፡
ስምምነቱን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ እና የነውማን ካፌ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ዴቪድ ነውማን ፈርመዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ከድርጅቱ ጋር መፈራረማቸው የሚድሮክ የቡና ምርታማነትን በማሳደግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት የሚጨምር መሆኑን ተናግረዋል።
የስምምነቱ አላማ በዋነኝነት የቡና ምርታማነትን መጨመር እና በሀገሪቱ የቡና እርሻ ልማትን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነም ገለፀዋል።
በተጨማሪም አቶ ጀማል ሚስተር ዴቪድ ነውማንን ኢትዮጵያን ከልባቸው የሚወዱና የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ታላቅ ሚና ያላቸው እንደሆኑ በመግለፅ አመስግነዋቸዋል።

ሚስተር ዴቪድ ነውማን በበኩላቸው ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር የተፈራረሙት የሁለትዮሽ ስምምነት ዘላቂነት ያለዉ እንደሆነና በቡና ሳይንስ ላይ አብሮ በመስራት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማስቻል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አክለውም በኢትዮጵያ የቡና ገበያ ዉስጥ ትልቅ ሚና እየተወጣ ከሚገኘው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር አብሮ ለመስራት በመስማማታቸው የተሰማቸውን ደሰታ ገለፀዋል።



የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተቀባይነት ካለው ነውማን ካፌ ግሩፕ ጋር መፈራረሙ የሀገሪቱን የቡና ምርታማነት የሚያሳድግና ለኢትዮጵያ ታላቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በስምምነቱ እጅግ መደሰታቸውን ገልፀዋል።








