ከ10 ሐገራት የተውጣጡ ከ130 በላይ የንግድ ትርዒት አቅራቢዎች የሚሳተፉበትና ከዛሬ ሰኔ 1 ጀምሮ እስከ ፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ቀናት የሚቆየው 5ኛው አግሮ ፉድ እና ፕላስት ፕሪንት ፓክ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል፡፡













በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግብርና ዘርፍ ስር የሚገኙና የተለያዩ የእርሻ ምርቶችን እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኤግዚቢሽኑ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን ያገኙትን የተቆላ ቡና ምርቶች የጣሳ እና ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት የሚያደርጋቸውን የተለያዩ የአትክልት አይነቶችንና ሌሎች የእርሻ ምርቶችን ለእይታ አቅርቧል፡፡
ከ3,000 በላይ የንግድ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙት የሚጠበቀው ይህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በግብርና’ በምግብ ማቀነባበሪያ በንጥረ ነገሮች በፕላስቲክ በሕትመትና በማሸጊያ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ለገበያ ትስስር ወቅታዊ የንግድ ዕድሎችን ለማወቅ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና መፍትሄዎችን ለማመላከት እንዲሁም በኢንዱስትሪው ውስጥ ስላሉ አዳዲስ ለውጦች ለማወቅ ጠቃሚ ዕድልን ይፈጥራል፡፡
ኢግዚቢሽኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ በክብር እንግድነት ተገኝተው የከፈቱት ሲሆን ዛሬን ጨምሮ እስከ መጪው ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡