ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከናወነው የ2015 ዓ.ም የታማኝ ግብር ከፋይ ሽልማት ነው በፕላቲኒየም ደረጃ ያሸነፈው።
ሽልማቱን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ከገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እጅ ተቀብለዋል።
ትናንት በተከናወነው በዚህ የሽልማት ስነ-ስርዓት ወቅት ድርጅቱ ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤትና እውቅና ደስተኛ መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
ታማኝ ግብር ከፋይነት በሚድሮክ የየዕለት የስራ አካል እንጅ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም ብለዋል አቶ ጀማል አህመድ።
ምንም እንኳን በሚሰሩት አቅም ልክ የሚከፍሉት የግብር መጠን ቢለያይም ሁሉም የሚድሮክ ድርጅቶች ግብርን በተገቢው ጊዜ እና በታማኝነት በመክፈል ግንባር ቀደም ሚናቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
በዚህም 18 የሚድሮክ አባል ድርጅቶች በነሐስ፥ በወርቅና በፕላቲኒየም ደረጃ በሀገር አቀፍ በተከናወነው የ2015 ዓ.ም የታማኝ ግብር ከፋይ ሽልማት ማሸነፋቸውን አስታውሰዋል።
ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በ2014 በጀት ዓመት የውጭ ምንዛሪ በማመንጨት ከማዕድን ዘርፍ እና በአጠቃላይ ከሁሉም የወጭ ምርት ላኪዎች 132 ሚሊየን ዶላር በማስገኘት በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአንደኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ እንደነበርም ይታወሳል።









