ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ክለቡ ያሰፈረማቸዉን ተጫዋቾች ሙሉ ወጪ በመሸፈን የምንግዜም አጋርነቱን በተግባር አሳይቷል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ያጋጠመውን የፋይናንስ ቀውስ ለመፍታት በቅርቡ የገንዘብ ድጋፍ ማድርጉም ይታወሳል።
ግሩፑ በዛሬው እለት ደግሞ ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲዘልቅና በጥንካሬው እንዲጓዝ ለማድረግ የአይቮሪኮስት፣ የኮንጎ ብራዛቪልና ሁለት የጋና ዜግነት ያላቸው አራት ተጨዋቾችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና ስፖርት ክለቡ ካጋጠመው የውጤት ቀውስ እንዲላቀቅ ታሪካዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክለቡ አንጋፋ ተጫዋችና የአሁኑ ጊዜያዊ የቴክኒክ የኮሚቴ ሰብሰቢ አቶ ሰለሞን መገርሳ እና የክለቡ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ፋሲል ተካልኝ ክለቡ ከነበረበት ችግር እንዲወጣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለሚያደርገው ድጋፍ ታላቅ ምስጋና አለን ብለዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ልዩ ረዳት አቶ ዘላለም ተፈራ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ክለቡን ወደ ነበረበት ገናናነት ለመመለስ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቡድኑን ለማጠናከር አራቱን ተጫዋቾችና የቀድሞውን የክለቡን አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን እንዲያደረግ ከዉጭ ማስመጣቱን ገልፀው ተቋሙ ለክለቡ የሚያደረገውን ድጋፉ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።
የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እና አቶ ጀማል አሕመድ በክለቡ የታሪክ ማህደር ላይ የማይሻር ታሪክ በማስቀመጣቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
90 አመታትን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ያሳለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የበላይ ጠባቂነትና በአቶ ጀማል አህመድ ጠንካራ ድጋፍ ወደ ቀደመ ዝናው ለመመለስ የተጫዋቾች መምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ – የሀገር ሀብት










