ዘርፉ ባለፉት ሳምንታት የ2018 በጀት አመት የስራ አፈጻጸምን ከእያንዳንዱ ድርጅት ጋር ሲገመግም ከቆየ በኋላ ሀምሌ 30 ቀን 2018 የሁሉም ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች፣ ሃላፊዎችና የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በተገኙበት የማጠቃለያ ግምገማ አድርጓል።
የግምገማ ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስር ያሉ ሁሉም ድርጅቶች የምርት እቅዳቸውን 112 በመቶ የፈጸሙ ሲሆን ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 52 በመቶ የምርት እድገት አለው። የሽያጭ አፈጻጸሙ ደግሞ የእቅዱን 109 በመቶ ሲሆን ከአምናው አፈጻጸም አንጻርም በ43 በመቶ እድገት እንዳለው ታይቷል።
ዘርፉ በበጀት አመቱ በሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣አዳዲስ ምርቶችን በማምረት፣ወደ ገበያ በማስገባት፣የምርት ጥራትን ከማሳደግ አንጻር፣አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት፣ የተያዙ የኢንቨስትመንት እቅዶችን መተግበር የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡ የታየ ሲሆን እነዚህን አፈጻጸሞች በቀጣዩ በጀት አመት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ማቀዱን ገልጿል።
በግምገማ መድረኩ በመገኘት ሂደቱን የመሩት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ያሉ ሁሉም ድርጅቶች ባለፉት አመታት እያሳኩ የመጡትን ውጤታማነት በ2018 በጀት አመትም ማስቀጠል መቻላቸው የመላ ሰራተኛውና የማኔጅመንት ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ጀማል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የታየው የምርት፣ የምርት ጥራት፣ የሽያጭ፣ የወጪ ቅነሳና ትርፋማነት ውጤታማነት የዚሁ አካል እንደሆነ በመግለጽ በዘርፉ ስር ባሉ ድርጅቶች ለመጣው ውጤት እውቅና ሰጥተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው የአቅም አጠቃቀም በተሻለ መፈጸም እንደሚገባው የገለጹ ሲሆን መጭው ጊዜ ጠንካራ ውድድር የሚኖርበት መሆኑን በመገንዘብ እራስን በአሰራር አጠንክሮ ለውጤት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በቅርቡ ወደ ዘርፉ የተቀላቀሉ ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ የተሰራውን ስራ በማድነቅ በቀጣዩ በጀት አመትም በ2018 ከተሰሩ ስራዎች በተሻለና ተወዳዳሪነትን በሚያሳድግ አግባብ ማኔጅመንቱ በትኩረትና በባለቤትነት መንፈስ እንዲሰሩ አደራ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል አቶ ጀማል አህመድ።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽንና ሪል ስቴት፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በንግድና በሆስፒታሊቲ ዘርፎች በመሰማራት ከአመታዊ ከትርፉ 10 በመቶ ለማህበራዊ ሃላፊነት በመመደብ እየሠራ የሚገኝ ታላቅ ተቋም ነው።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ – የሀገር ሀብት









