ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በስሩ 19 ድርጅቶችን ያቀፈና በሐገራችን ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አወንታዊ አሻራ እያሳረፈ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዘርፉ ስር ያሉ ድርጅቶች በበጀት ዓመቱ ለመሸጥ ያቀዱት 10.89 ቢሊዮን ብር ሲሆን የብር 12.21 ቢሊዮን ሽያጭ በማከናወን የእቅዳቸውን 112 በመቶ ለማሳካት ችለዋል፡፡
ይህም አፈፃፀም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ66 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን ለሀገር ከፍተኛ ግብር በማስገባትም የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ሆነዋል፡፡
እያስመዘገቡ ላሉት ከፍተኛ እድገትና እመርታ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላሉ ሰራተኞች እና አመራሮች በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የእውቅና መስጠትና በስራ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ኮከብ ሰራተኞች እና አመራሮችም የሰርተፊኬት እና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ “እኛ የፋብሪካው ባለቤቶች ነን፤ ስለሆነም የፋብሪካው ቀጣይ እድገትና ብልፅግና በእኛው በባለቤቶቹ ጥረትና ትጋት ላይ የተመሠረተ ነው!” በሚል መርህ በመንቀሳቀሳችሁ እና በባለቤትነት ስሜት በመስራታችሁ ለታላቅ ውጤት በቅታችኋልና ይህን መርህ አጠናክራችሁ በመቀጠል ከዚህም የላቀ ውጤት እንድታመጡ በርትታችሁ ስሩ በማለት ሰራተኛውን አበረታተዋል፡፡
የተቋሙ ባለቤትና ሊቀመንበር በሰጡን አቅጣጫ መሠረት የተገኘውን ትርፍ ድርጅቶቹን ይበልጥ ለማዘመን እና ለማስፋፋት እንዲሁም የሰራተኛውን ሕይወት ለመቀየር እናውለዋለን ያሉ ሲሆን በቀጥይም ለበለጠ ስኬት እንነሳ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አካወለድ አድማሱ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም በ2013 እና 2014 ለሁለት

ጊዚያት “ያህል በውስን ሰራተኛ ብቻ እንዲህ አይነት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር መደረጉን አውስተዋል፡፡
የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው ሁሉም የየድርጅቶቹ ሰራተኞችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ በዓሉ እንዲዘጋጅ የተደረገው ሰራተኛው እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅና ድርጅቶችም ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንዲያገኙ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ይህ አይነቱ የእውቅና እና የሽልማት ዝግጅት ቀጣይነት ያለው እንደሆነ በማንሳት ድርጅቶች እርስ በእርስ በቀና መንፈስ በመወዳደር ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉና በመደጋገፍ አብረው እንዲሰሩ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው በዚህ የእውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር ላይ 6 ሺህ ያህል ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በላቀ አፈፃፀም እና ራሱን ከኪሳራ በማውጣት ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበው ላሜ ዴየሪ ኃ.የተ.የግ.ድርጅት ልዩ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በዘርፉ ስር የሚገኙት ድርጅቶችም ምርት እና አገልግሎታቸውን የሚያስቃኝ ኢግዚቢሽን አሳይተዋል፡፡






