በዘርፉ ስር ያሉ ድርጅቶች እርስ በእርስ እንዲሁም ከሌሎች በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ካሉ ድርጅቶች ጋር ተደጋግፈው መስራታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገልጿል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ነሐሴ 3/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና ዘርፍ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የውይይት መድረክ አካሂዷል።
ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 3/2015 ዓ.ም ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ማሰልጠኛ ማዕከል በተካሔደው የውይይት መድረክ ላይ በግብርና ዘርፍ ስር የሚገኙ ሁሉም የስራ አመራሮች ተሳትፈዋል።
በዚህ መድረክ ላይ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ችግሮች በስፋት የተዳሰሱ ሲሆን ለ2016 በጀት ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮችም ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ታደሰ ውይይቱን የመሩ ሲሆን
በውውይቱም ላይ:-
- በዘርፉ ስር ያሉ ድርጅቶች እርስ በእርስ እና ከሌሎችም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ካሉ ድርጅቶች ጋር ተደጋግፈው መስራታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ፤
- ተቋማቱ ያላቸውን እምቅ አቅም መጠቀም ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉ፤
- ስርቆትንና የምርት ብክነትን ለማስቀረት ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲሰራ፤
- ድርጅቶች የተቋማቸውን ሲስተም መዘርጋትና የሰራተኛውን አቅም መገንባት ላይ የበለጠ እንዲሰሩ፤
- ምርታማነትና ጥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ፤
- ወጪ ቅነሳ ላይ እንዲሰሩ፤
- የስራ ከባቢን ሳቢ በማድረግ ለሠራተኞቻቸው ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩ፤
- ተቋማቱን የበለጠ ትርፋማ እንዲያደርጉ፤
- የፋይናንስ መመሪያዎችን ለሠራተኛው እንዲያርዱና በየወቅቱ ተገቢውን የኦዲት ስራ እንዲያስቀጥሉ የሚሉት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በመሆናቸው ሰፊ ጊዜ ተሰጥቷቸው ሀሳብ ተንሸራሽሮባቸዋል።በድርጅቶቹ መስማማት ተደርሶባቸው ሁሉም ለተፈጻሚነታቸው እንደሚሰሩም ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግብርና ዘርፍ የኮርፖሬት ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ሞገስ በበኩላቸው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።
እነርሱም:- - የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሞክሮን በመውሰድ በድርጅቶች መካከል ቀና የውድድር መንፈስ እንዲኖር መስራት፤
- ለአትክልትና ለአበባ ምርቶች ተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ የገበያ መዳረሻዎችን መፈለግና መላክ፤
- በሁሉም ድርጅቶች የተጠናከረ የወጪ ቁጥጥር ስርዓት ስትራቴጂ በመፍጠር ጤናማ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖር ማስቻል፤
- በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተያዙ የፕሮጀክት ስራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና ወጪ ማጠናቀቅ፤
- የግብርና ምርቶችን በጥራት በማምረት ለሀገር ውስጥና ለዓለም ዓቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የዘርፉ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ታደሰ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር “ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሀገር ነው፤ ሀገር ደግሞ ማደግ አለባት፤ ስለዚህም ሁላችንም ሀገር እንደሚመራ መሪ በመሆን በበጀት አመቱ ያገኘናቸውን ስኬቶች አጠንክረን በመቀጠል ሀገራችንን ማሳደግ ይኖርብናል” ብለዋል።


በተለይም እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ውጤታማ ሥራዎችን ያከናወኑትንና የመሩትን የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንደስትሪ አመራሮችና መላ ሰራተኞች ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ፈለቀ ታደሰና ተሳታፊዎች በሙሉ ቆመው በልዩ ስሜት አመስግነዋል።
የግብርና ዘርፉ ባሳለፍነው የ2015 በጀት ዓመት የ9.8 ቢሊዮን ብር ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን ለመንግስት የሚጠበቅበትን ግብር 1.8 ቢሊዮን ብር ገቢ አድርጓል። በዘርፉ ስር የሚገኙት 6 ድርጅቶች ብቻ ለማህበራዊ ኃላፊነት ስራዎች 52.3 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገዋል።
የግብርና ዘርፍ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ካሉ 6 ዘርፎች መካከል አንዱ ሲሆን በስሩ ስድስት ድርጅቶችን ይዟል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አጠቃላይ ከ71 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ የግብርና ዘርፉ ብቻ ከ48,000 በላይ ለሆኑ ሠራተኞች የስራ ዕድል ፈጥሯል።
