ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ አቶ አብነት ለቦሌ ታወርስ ህንፃ ግንባታ ለማዋል በሚል ከባንክ ከተበደሩት 425 ሚሊየን ብር ውስጥ ለተባለለት ዓላማ አለመዋሉ የተረጋገጠው 304 ሚሊየን ብር ለማህበሩ እንዲመለስ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ
ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ
ስፋታቸው 3,383 እና 1,971 ካሬ ሜትር የሆኑ እና ስያሜያቸው C እና D የተባሉ የካርታ ይዞታዎች ለቦሌ ታወርስ ማስፋፊያነት የተሰጡ ሆነው ሳለ የኩባንያው ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አብነት ገ/መስቀል የቦሌ ታወርስ ኃ.የተ.የግ.ማ. ስምን ከካርታዎቹ ላይ እንዲወጣ በማስደረግና የግል ንብረቴ ነው በማለታቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሃ ብሔር ችሎት ችሎት ክስ አቅርበን ስንከራከር ቆይተናል፡፡
በዚሁ መሰረት የማህበሩ የቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግማ 60 በመቶ ባለድርሻ የሆኑት ሼይኽ መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በአቶ አብነት ገብረመስቀል ላይ ያቀረቡትን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤት በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ፍርድ ሰጥቷል፡፡
በዚሁ ፍርድ መሰረት ፍ/ቤቱ ሼይኽ መሀመድ ያቀረቡትን ክስ ሙሉ በሙሉ በመቀበል ተከሳሽ አቶ አብነት ገ/መስቀል ከህግ ውጪ የግሌ ነው በማለት በህገወጥ መንገድ ካርታ ያወጡባቸውን የኩባንያውን ከላይ የተጠቀሱ 2 ይዞታዎች ለማህበሩ ተመላሽ እንዲያደርጉ በማለት በመ/ቁ/276347 ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አብነት ገ/መስቀል የኩባንያውን ህንፃ ግንባታ ለማሰራት በሚል በማህበሩ ስም ከባንክ የተበደሩትን 425 ሚሊየን ብር ለኩባንያው ህንፃ ግንባታ ማዋል ሲገባቸው ብድሩ ከተፈቀደለት ዓላማ ውጪ ለተለያዩ ግለሰቦች እንዲተላለፉ በማድረግ በማህበሩ ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
አቶ አብነት ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ የኩባንያው 60 በመቶ ባለድርሻ የሆኑት ሼይኽ መሀመድ ክስ አቅርበዋል፡፡
ክሱን ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤት የብድሩ ገንዘብ ለኩባንያው ህንፃ ግንባታ መዋል አለመዋሉን የሚያጣሩ ኦዲተሮች ሾሞ ኦዲተሮቹ ያጣሩት ሪፖርት ለፍ/ቤት ቀርቦለታል፡፡
ፍ/ቤቱም ኦዲተሮቹ ያቀረቡለትን ሪፖርት ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ፍርድ አቶ አብነት ገ/መስቀል 304 ሚሊየን ብር ከባንክ ወለድ ጋር ለኩባንያው እንዲከፍሉ በማለት በመ/ቁ/276542 ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ በዋሉ ሌሎች ሁለት ችሎቶች ደግሞ……….
አቶ አብነት ገ/መስቀል ከቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ ስራ አስኪያጅነት እንድነሳ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የተወሰነብኝ ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 243549 የሰበር አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የሰበር ሰሚ ችሎት አቶ አብነት ገ/መስቀል ከስራ አስኪያጅነት እንዲነሱ የተወሰነው በበቂ ምክንያት ነው በማለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ አጽንቶታል፡፡
በተጨማሪም አቶ አብነት ገ/መስቀል ከስራ አስኪያጅነት እንዲነሱ ከተፈረደባቸው በኋላ በምትካቸው አምባሳደር አሊ ሱለይማን የቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ ስራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል፡፡ አቶ አብነት ይህን ሹመት በመቃወም ፍርድ ቤት ክስ አቅርበው ነበር፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሃብሄር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት አምባሳደር አሊ ሱለይማን በስራ አስኪያጅነት የተሾሙት ህጉን ተከትለው ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔን አጽንቶታል፡፡