የወደፊቱ የከተማችን ጌጥ እና ግዙፍ የመኖሪያ መንደር የሚሆነውን የመኖሪያ መንደር የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ ለማየት በዛሬው ዕለት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
በግንባታ ሂደቱ ላይ የኮንስትራክሽን ስራውን እያካሄዱ ያሉት የሚድሮክ ኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ፣ የሜፖ ኮንትራክቲንግ እና ማኔጅመንት ሰርቪስስ ኃ/የተ/የግ/ማ እና የዲዛይን እና ሱፐርቪዥን ስራውን የሚያከናውነው ዚያስ ኢንተርናሽናል አርክቴክቸር እና ኢንጂነሪንግ የስራ ኃላፊዎች በጉብኝቱ ላይ ተገኝተው ስለ ስራ ሂደቱ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የአመራር ለውጥ አድርጎና በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ወደ ስራ ከገባበት ወቅት ጀምሮ በስሩ ያለውን የሰው ኃይል እና ሃብት በአንድነት አቀናጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ በመሆኑ የመሐመዲያ ቪሌጅ የመኖሪያ መንደር ግንባታም በላቀ አፈፃፀም ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡



ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድም ግንባታው በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው ግንባታውን በእቅዱ መሠረት ለማጠናቀቅ በዋና መስሪያ ቤቱ በኩል አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
መሐመዲያ ቪሌጅ አሁን ባለበት ደረጃ ለ660 ሰራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በዚህ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የመኖሪያ መንደር ቪላዎች፣ የመኖሪያ አፓርታማ፣ ሆቴል፣ፕላዛ፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሞል፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ 8,800 ያህል የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ፣ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆነ የህዝብ መዝናኛ ያካተተ ሲሆን ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ውበት የሚሆን የመኖሪያ መንደር ይሆናል።
የግንባታው ባለቤት ሁዳ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማ ሲሆን ዚያስ ዲዛይን ኢንተርናሽናል የዲዛይን እና የሱፐርቪዥን ስራውን ያከናውናል፡፡
በከተማ ውስጥ ሌላ ከተማ ለመገንባት ጳጉሜን 5/2014 ዓ.ም የመሐመዲያ ቪሌጅ መሠረት ድንጋይ መጣሉ ይታወሳል፡፡








