የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው አህፋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለስልጠና የሚውሉ የስፖርት ትጥቅና መገልገያዎችን አበርክቷል።
ድጋፉን የአህፋ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራህማን አህመድ ለክለቡ ጊዜያዊ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነሲቡ ጫኮና ዋና አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን (ሚቾ) አስረክበዋል።
የአህፋ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራህማን አህመድ፤ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የይድነቃቸው ተሰማ የታዳጊዎች አካዳሚ ውስጥ ላለው ክሊኒክ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ ዛሬም ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የስፖርት ትጥቅና መገልገያዎች በማበርከት ሁልጊዜም ከክለቡ ጎን መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
የክለቡ ጊዜያዊ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነሲቡ ጨኮ አህፋን ጨምሮ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለክለቡ ስኬት ቀጣይነት ባለው መልኩ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን (ሚቾ) በበኩላቸው፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ክለቡ አጋጥሞት ከነበረው ችግር እንዲወጣ የአንበሳውን ሚና በመወጣቱ ምስጋናቸውን በማቅረብ፤ ዛሬ የተደረጉት የስፖርት ቁሳቁሶች ተጫዋቾች በስልጠና ወቅት ሙሉ ትጥቅ አሟልተው እንዲሠሩ ያግዛሉ ብለዋል።
ሚቾ አክለውም ሚድሮክ ያበረከተልንን ድጋፎች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ተጫዋቾች ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ በማድረግ፣ ክለቡን ለውጤት አብቅተን ደጋፊዎችን ለማኩራት እንሰራለን ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለስፖርት ክለቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ክለቡን ወደ ነበረበት የቀድሞ ገናናነቱ ለመመለስ የተለያዩ ተግባራትን እያደረገ ይገኛል፡፡
አህፋ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ውስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች አንዱ ሲሆን በምግብ ማቀነባበር፣ በትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስመጣትና በንግድ ስራዎች ላይ የተሰማራ ኩባንያ ነው።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ – የሀገር ሀብት









