ባለሙያዎቹ ትምህርታቸውን ይከታተሉባቸው በነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉና የተቋሙን የመግቢያ ፈተና ወስደው ያለፉ ተማሪዎች ናቸው።
እነዚህ ባለሙያዎች በአግሮኖሚ፣ በሆርቲካልቸር፣ በፕላንት ሳይንስ፣ በአካውንቲንግ፣ በኮምፒውተር ሳይንስ፣ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ እና በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ናቸው።
ባለሙያዎቹ ለሁለት ሳምንታት የተለያዩ የተቋማዊ ባህል፣ እሴቶች እንዲሁም የተግባር ሥልጠናዎችን የወሰዱ ሲሆን፣ በግብርና ዘርፍ ስር በሚገኙት ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ እና ኢትዮ አግሪ ሴፍት ድርጅቶች ላይ ተመድበው፣ ለሁለት ወራት የሥራ ላይ ሥልጠናም የሚቀጥሉ ይሆናል።
ይህም ለእውቀት ሽግግርና የተማረ የሰው ኃይል ለቀጣይ የድርጅቱ አመራር ተተኪ ትውልድን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ታደሰ አዲስ ወደ ሥራ የተሰማሩት ባለሙያዎች በትምህርትና በሥልጠና ያገኙትን እውቀት በተግባር በማሳየት ለዘርፉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ልምድና አዲስ እውቀት ሲደመሩ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ስለሚያስችል፣ በሥራ ቦታቸው የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በቡድን በመሥራት የተሻለ ምርታማነት ለማምጣት መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ ‘የድርጅቱ ባለቤቶች እኛ ነን’ በሚል መርህ ቃል በትጋት በመሥራት፣ ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው የቡና፣ ሻይና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ምርታማነት በማሳደግ ተቋሙን ለትውልድ ለማሸጋገር በትጋት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ሚድሮክ ለሰጣቸው ዕድል በማመስገን፣ ለሀገር በሚሠራው ተቋም ውስጥ ለመሥራት ያገኙትን ዕድል በመጠቀም የሀገር ማልማት ዓላማውን ለማሳካትና ለትውልድ የሚሸጋገር ተቋም የመገንባት ሂደት ውስጥ ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሀገርን ለማሳደግ ከሚሠራባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች መካከል ግብርና አንዱ ሲሆን፤ ዘርፉን በማዘመን፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለመጨመር፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በስፋት በመሥራት ላይ ይገኛል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽንና ሪል ስቴት፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በንግድና በሆስፒታሊቲ ዘርፎች በመሰማራት ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ግዙፍ ተቋም ነው።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዓመታዊ ትርፉ 10 በመቶውን በመመደብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።










