የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፐርት ክለብ ከፍተኛ የክለቡ አመራሮች፣የስፖርት ስራ ሃላፊዎች፣የቦርድ አባላትና ተሳታፊዎች በተገኙበት በሸራተን አዲስ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አንጋፋ ቡድን መሆኑን ጠቅሰው በቅርብ አመታት ከገጠሙት ፈተናዎች ወጥቶ ጥሩ አቋም ላይ መገኘቱ አስደሳች ነው ብለዋል።
ክለቡ በኢትዮጵያ እግርኳስ አንጋፋ ስም ያላቸው ተጫዋቾችንና የስፖርት ቤተሰቦችን ያፈራ ክለብ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባልም ብለዋል።
አቶ ባህሩ የክለቡን ፈተናዎች በመገምገም ወቅታዊ አቋሙ ላይ እንዲገኝ ላደረጉት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕና የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ያላቸውን ከፍ ያለ ምስጋና ገልጸዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የ5 ወራት የስራ አፈጻጸም ሂደት ሪፖርት ያቀረቡት የክለቡ ሊቀመንበር አቶ ነሲቡ ጫኮ በበኩላቸው ክለቡን ከገጠመው ፈተና ለማስወጣት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹ ሲሆን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአንድ አመት ውስጥ 200 ሚሊየን ብር መለገሱን አስታውቀዋል።
አክለውም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለክለቡ እያበረከተ ያለው ሚና በቃላት አይገለጽም ያሉት አቶ ነሲቡ ጫኮ ድርጅቱ ለክለቡ አለምዓቀፍ መመዘኛን ያሟላ ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት ጥናቱን አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷልም ብለዋል።
በተጨማሪም አቶ ነሲቡ ይህ አይነቱ የአጋርነት ስምምነት ለአንጋፋው ክለብ ዳግም ማንሰራራት ሚናው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
ሊቀመንበሩ ክለቡ በታደጊዎች ልማት ላይ፣በስፖርት መሰረተ ልማት፣ ተጨማሪ ገንዘብ በማግኘትና በሌሎች ወሳኝ ዘርፎች ላይ የተሰሩ ሰራዎችንም አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 200 ሚሊዮን ብር፣ የሞሀ ለስላሳ መጠጦች አክሲዮን ማህበር ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ዳሸን ባንክ 200 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ቢጂአይ ኢትዮጵያ 50 ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ለስፖርት ማህበሩ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ከአህፋ አንድ አውቶብስና አንድ ሚኒባስ ለክለቡ በስጦታ ተበርክቶለታል።
እንዲሁም ሞጆ ላይ የሚገኘው አሮሰ ሆቴል ለስፖርት ክለቡ ተሰጥቷል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና አላማ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የኢትዮጵያን ዋንጫ እንዲበላ ሳይሆን በአፍሪካ ገናና ቡድን ማድረግ ነው ያሉ ሲሆን እስካሁን ለተደረጉ ድጋፎች በሙሉ ሼኽ መሃመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል ያሉት አቶ ጀማል ከቤኔፊካ የስፖርት አካዳሚ ጋር ግንኙነት መፍጠሩና የቢሾፍቱ አካዳሚ ላይ የጀመርነው ስራ ለዚህ ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ለቀጣይ ስራዎችም ምክክርና ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በተጨማሪም የክለቡ የ8 አመት ኦዲት ሪፖርት ቀርቦ በአንድ ድምጽ ተዓቅቦ የጸደቀ ሲሆን ላለፉት 5 ወራት በስራ ላይ የነበሩት የቦርድ አባላት እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በኮንስትራክሽንና ሪል ስቴት፣ በሆስፒታሊቲና በንግድ ዘርፎች የተሰማራ ሲሆን ከ80ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረና ከአመታዊ ትርፉ 10 በመቶውን ለማህበራዊ ሃላፊነት እያዋለ የሚገኝ ግዙፍ ሃገራዊ ተቋም ነው።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ – የሀገር ሀብት










