በጉብኝቱ ወቀት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ማምረቻ ስርዓት ለኢትዮጵያ ትልቅ በረከት ስለሆነ ህዳሴ ነው ማለት እንችላለን ብለዋል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና ዘርፍ አካል የሆነው የኤልፎራ ሻሎ እርሻ በሰብል ምርትና የዶሮ ልማት አስደናቂ ስራዎችን በመስራትና በሀገሪቱ “የሌማት ትሩፋት” ፕሮጀክት ውስጥ ሀገርን የሚያኮራ ተግባር እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም እንደ ሀገር በ2015 ዓ.ም 40 ሚሊዮን በ2016 ዓ.ም ደግሞ 80 ሚሊዮን ዶሮዎችን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ቁጥር ሃገሪቱ ካላት አጠቃላይ የህዝብ ብዛት አንፃር በቂ ባለመሆኑ መሰል ስርዓቶች መዘርጋታቸው ተገቢና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አስገንዘበዋል።

በ2017 ዓ.ም ከሌሎች ስራዎች በተጨማሪ ኤልፎራ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቅድመ ወላጅ (Grandparent) ዶሮዎች ስርዓትን ወደ ስራ በማስገባት በአጠቃላይ 150 ሚሊዮን ዶሮዎችን በማምረት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዝግጅት መጠናቀቁን አብስረዋል።
ይህን ቴክኖሎጂ በሀገራችን ማስጀመር ቀላል ስራ ባይሆንም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ቁርጠኝነትና በመላ አመራሩና ሰራተኛው ብርታት መሳካቱን ገልፀው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፕሮጅክቱ የዉጪ ምንዛሪን በማስቀረትና የሌማት ትሩፋትን በመደገፍ በኩል ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።


በጉብኝቱ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ደስታ ሊዳሞ፥ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፥ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግብርና ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።







