የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አካለወልድ አድማሱ ጥራትን ለመጠበቅ እያደረጉ ላለው ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ እዉቅና ሰጥቷቸዋል ።
እዉቅናዉ የተሰጣቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ መብራት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ሆራይዘን አዲስ ጎማ ማኑፋክቸሪንግን በጎበኙበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት አቶ አካለወልድ በሚመሩት ዘርፍ ስር ያሉ ድርጅቶች ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲሰሩ በማድረጋቸው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት አምባሳደርነት ይገባቸዋል ብለዋል።
ሥራ አስፈፃሚው የድርጅት ኃላፊዎች በፋብሪካዎች ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ በማስቻል ዉስጥ የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልፀው አቶ አካለወልድ ጥራትን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ለሌሎች አመራሮችም ምሳሌ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ መብራት፥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የኢትዮጵያ ምርት እንዲኖራቸው ማስቻል የድርጅቱ ግብ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ለአብነትም ታህሳስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቁ ቤተ-መንግስት በተካሄደው ሀገር ዓቀፍ የጥራት ሽልማት ላይ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ሆራይዘን አዲስ ጎማ በጥራት ከተወዳደሩ 47 ድርጅቶች መካከል ብቸኛው አንደኛ ደረጃ የልህቀት ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በጥቅሉ 20 የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድርጅቶች ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማቱን አግኝተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ሆራይዘን አዲስ ጎማን ጨምሮ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስር ያሉ 14 ድርጅቶች በ1ኛ የልህቀት ዋንጫ፣ በከፍተኛ አድናቆት፣ በአድናቆትና በተሳትፎ ደረጃዎች ማግኘታቸው አይዘነጋም።








