ሁለቱ ተቋማት በግብርና ዘርፍ-በሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ፣ዶሮ እርባታ በማዕድን ዘርፍ- ሶዳአሸ እና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች በጋራ ለመስራት የፊርማ ስነ-ስርዓት አድርገዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የኦሮምያ ሶቨሪን ፈንድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አደሬ አሰፋ እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ ፈርመዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚድሮክ ሊቀ-መንበር ሸኽ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ለሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸዉ በማለት በተለይም ሚድሮክ ለኦሮሚያ ክልል እድገት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የዛሬው ስምምነትም በግብርናና በማዕድን ዘርፎች ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ በጋራ በመስራት ለሀገር እድገት የበለጠ አሰተዋጽኦ ለማበርከት ያለመ እንደሆነ ርእሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ ሚድሮክ ስምምነት በተደረገባቸው የልማት መስኮች በተለያዩ አከባቢዎች በመስራት የሀገር ኢኮኖሚን ከማሳደግ ባሻገር ሀገር በቀል የኢኮኖሚክ ሪፎርምን ለማሳካት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዛሬ የተደረገዉ ስምምነትም በሀገር እድገት ዉስጥ የሚድሮክን ድርሻ የበለጠ የሚያጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኦሮምያ ሶቨሪን ፈንድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አደሬ አሰፋ በበኩላቸው በሀገሪቱ ከግሉ ዘርፍ ግዙፍና ዘርፍ ብዙ ከሆነው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመሆን የክልሉን እድገት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።









